የኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ባለሙያዎች ማህበር “የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሸሪዓ አማካሪዎች ዓመታዊ ጉባኤ” አካሔደ

(አዲስ አበባ ፡ የካቲት 18 ቀን 2015) የኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ባለሙያዎች ማህበር ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ
ምክር ቤት የዑለሞች ጉባኤ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን “የኢትዮጵያ የሸሪዓ አማካሪዎች ዓመታዊ ጉባኤ” ቅዳሜ የካቲት 18
ቀን 2015 በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ “ዛጉዌ” የመሰብሰቢያ አዳራሽ ‘የሸሪዓ አማካሪዎች የጋራ ምክክር ለተሟላ የወለድ ነጻ አገልግሎት’
በሚል መሪ ቃል አካሄደ።
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ጉባኤ ጽ/ቤት አባላትና አመራሮች፣ በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት
ውስጥ በሸሪዓ ማማከር ላይ የተሰየሙ የሸሪዓ ምሑራን፣ የተለያዩ የባንክ፣ የኢንሹራንስና የፋይናንስ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች፣ ከወለድ ነፃ
የፋይናንስ የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ተቋማት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የማህበሩ አባላት ተገኝተዋል።
የማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ እርስቱ ከማል ባስተላለፉት ‘የእንኳን ደህና መጣችሁ’ መልዕክት ማህበሩ ይህንን የሸሪዓ
አማካሪዎች ጉባኤ ለማካሄድ ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት በሁሉም የፋይናንስ ተቋማት የሚሰሩ የሸሪዓ አማካሪዎች ለዘርፉ ሁለንተናዊና ዘላቂ
እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበትን እንዲሁም በሸሪዓ እና በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ የሚወያዩበትን ዓመታዊ የምክክር
መድረክ ለማዘጋጀት እንደሆነ ገልጸዋል። በተጨማሪም ጉባኤው በየዓመቱ ቀጣይነት እንደሚኖረው ቃል ገብተዋል። በሌላ በኩል ጉባኤው
በተለያዩ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ተቋማት ለሚሰሩ የሸሪዓ አማካሪዎች የመተዋወቂያ መድረክ እንዲሆንና እርስበርስ የልምድ ልውውጥ
ለማካሄድ እንዲያመች ተብሎ እንደተዘጋጀ ገልጸው በዝግጅት ሂደቱ ላይ ለተሳተፉ እንዲሁም ጥሪውን አክብረው በጉባኤው ላይ ለተገኙ
ታዳሚያን ምስጋናቸውን አቅርበው፤ ጉባኤው የተሳካ ይሆን ዘንድም የሁሉም ታዳሚ ንቁ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።
በመቀጠልም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለሞች ጉባኤ ም/ሠብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ጄይላን ጉባኤውን በንግግር
ከፍተዋል። ዶ/ር ጄይላን በመክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደገለጹት በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ተሰይመው የሚገኙ የሸሪዓ አማካሪ ምሁራን
ተቀራርበው በመስራት ወጥነት ያለው የሸሪዓ አስተዳደር እና የፈትዋ አሰጣጥ ስርዓት በሀገራችን እንዲኖር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ
ጥሪ አቅርበዋል። በዚህም ረገድ በባንክ እና ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሠማሩ ባለሙያዎች ተገቢዉን ድጋፍ እና ግብዓት በመስጠት አንዲተባበሩ
ጥሪ አቅርበዋል። በመጨረሻም፣ በሀገራዊ ደረጃ የማእከላዊ የሸሪዓ ቦርድ መቋቋምን አስፈላጊነትን አፅንዖት ሰጥተው ንግግራቸውን
አጠናቀዋል።

በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ባለሞያዎች ማህበር ጠቅላላ ጉባዔ ፀሀፊ የሆኑት አቶ መስፍን በዙ ማህበሩን መመስረት
ያስፈለገበትን ምክንያት፣ የምስረታ ሂደቱን፣ የተቋቋመበትን ዓላማ እና ማህበሩ ከምስረታ ጊዜው ጀምሮ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት
ለታዳሚው በማብራራት የማህበሩን አላማ ለሚደግፉ ግለሰቦች እና ተቋማት የአብረን እንስራ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም አቶ ኑሪ
ሁሴን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ም/ፕሬዝዳንት ዘርፉ ያለፈበትን ሂደትና አሁን የደረሰበትን ደረጃ
አብራርተዋል። ከሸሪዓ አማካሪዎች ጋር በተያያዘም ኢንዱስትሪው ላይ እየታዩ ያሉ ተግዳሮቶችን ጠቅሰው ለመፍትሄው ሁሉም ባለድርሻ
አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንዲሚገባ አሳስበዋል። በሌላ በኩል ወ/ሮ ኢልሃም አቡበከር፣ የግሎባል ኢንሹራንስ
የተካፉል (እስላማዊ ኢንሹራንስ) ዘርፍ ሃላፊ በበኩላቸው በሀገራችን የተካፉል አገልግሎት አጀማመር እና አሁን የደረሰበትን ደረጃ
ለጉባኤው ተሳታፊዎች አብራርተዋል።
የማህበሩ ፕሬዘደንት የሆኑት አቶ ኢብራሂም ዳውድ በመቀጠል የጉባኤው አበይት ርዕስ የሆነውን “የሸሪዓ ቁጥጥር አስፈላጊነትና የሸሪዓ
አማካሪ ኮሚቴ ሚና” ላይ የተዘጋጀ ጥናታዊ ፁሁፍ አቅርበዋል። በዚህ ጥናታዊ ፁሁፍ ውስጥ የሸሪዓ ቁጥጥር አስፈላጊነት፣ መርሆቹ፣
ዝርዝር ሒደቶቹ፣ የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ ስራ እና ኃላፊነቶች እንዲሁም የሸሪዓ አማካሪ ኮሚቴ የአሰራር ሂደቶች በስፋት ተዳሰዋል።
በተጨማሪም አቶ ኢብራሂም በጥናታዊ ፁሑፋቸው ላይ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮዎችን፣ በዓለም ላይ እየተተገበሩ ስላሉ የሸሪዓ አስተዳደር
መስፈርቶች እና በሀገራችን በተለያዩ ተቋማት ስላለው የሸሪዓ አስተዳደር ማእቀፍ፣ መልካም ተሞክሮዎች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ ሰፊ ገለፃ
አድርገዋል። በቀጣይ በሀገራችን እያደገ ላለው ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ዘላቂነት ጉልህ ጠቀሜታ ስለሚኖረው አጠቃላይ የሸሪዓ
አስተዳደር ማእቀፍን በተመለከተም ይበጃል ያሉትን ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል።
በመቀጠልም በጉባኤው ላይ በቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍ እና በተደረጉት ንግግሮች ላይ ተመስርተው የጉባኤው ታዳሚያን የተለያዩ ጠቃሚ
አስተያየቶችና ጥያቄዎች አቅርበዋል። በተለይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማ ጉባኤ አባላት ከወለድ ነጻ
የፋይናንስ አገልግሎትን በተመለከተ በጉባኤው ስር ኮሚቴ እንደተቋቋመ አሳውቀው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከዚሁ ኮሚቴ ጋር በቅርበት
እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። የማህበሩ ስራ አመራር አባላትም በታዳሚያን የቀረቡትን አብዛኛዎቹን አስትያየቶች ለቀጣይ ስራዎች
በግብዓትነት መውሰዳቸውን ገልጸው ለቀሪዎቹ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተጨማሪም የማህበሩ አመራር
አባላት ማህበሩ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል በዑለሞች ጉባኤ ስር ለተቋቋመው ኮሚቴ የሚጠበቅበትን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያበረክት ቃል
ገብተዋል።
በመጨረሻም ጉባዔው የዘምዝም ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሆኑት ወ/ሮ መሊካ በድሪ የማጠቃለያ ንግግር ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የፋይናንስ ባለሙያዎች ማህበር ለትርፍ ያልተቋቋመ ማህበር ሲሆን የካቲት 11 ቀን 2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበራት
ድርጅቶችና ኤጀንሲ መዝገብ ቁጥር 5456 ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ የሙያ ማህበር ነው። ለበለጠ መረጃ የማህበሩን ድረ ገጽ ይጎብኙ
www.eiffpa.com

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *